Job 7

1“የሰው ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ተጋድሎ አይደለምን?
ዘመኑስ እንደ ምንደኛ ዘመን አይደለምን?
2የምሽትን ጥላ እንደሚመኝ አገልጋይ፣
ደመወዙንም እንደሚናፍቅ ምንደኛ፣
3እንዲሁ ከንቱ ወራት ታደሉኝ፣
የጕስቍልና ሌሊቶችም ተወሰኑልኝ።
4በተኛሁ ጊዜ ‘መቼ ነግቶ እነሣለሁ?’
እላለሁ፤ ሌሊቱ ይረዝማል፤ እስኪነጋም እገላበጣለሁ።
5አካሌ ቈስሎ ትልና ቅርፊት ለብሷል፤
ቈዳዬ አፈክፍኳል፤ ቍስሌም አመርቅዟል።

6“ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይፈጥናል፤
ያለ ተስፋም ያልቃል።
7ሕይወቴ ትንፋሽ ያህል እንደ ሆነች ዐስብ፤
ዐይኔም ከእንግዲህ ደስታን አያይም።
8አሁን የሚያየኝ ሰው ዐይን ከእንግዲህ አያየኝም፤
ትፈልገኛለህ፤ እኔ ግን የለሁም።
9ደመና በንኖ እንደሚጠፋ፣
ወደ መቃብር
የዕብራይስጡ ሲኦል ይላል።
የሚወርድም አይመለስም።
10ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፤
ስፍራውም ከእንግዲህ አያውቀውም።

11“ስለዚህ ከቶ ዝም አልልም፤
በመንፈሴ ጭንቀት እናገራለሁ፤
በነፍሴም ምሬት አጕረመርማለሁ።
12በላዬ ጠባቂ ታደርግ ዘንድ፣
እኔ ባሕር ነኝን ወይስ የባሕር አውሬ?
13ዐልጋዬ ያጽናናኛል፣
መኝታዬም ማጕረምረሜን ይቀንስልኛል ባልሁ ጊዜ፣
14አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፤
በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤
15ስለዚህ እንዲህ ሆኖ ከመኖር፣
መታነቅና መሞትን እመርጣለሁ።
16ሕይወቴን እጸየፋለሁ፤ ዘላለም መኖር አልፈልግም፤
ዘመኔ እንደ እስትንፋስ ነውና ተወኝ።

17“ከፍ ከፍ ታደርገው ዘንድ፣
ልብህንም ትጥልበት ዘንድ ሰው ምንድን ነው?
18በየማለዳው ትመረምረዋለህ፤
በየጊዜውም ትፈትነዋለህ።
19ዐይንህን ከእኔ ላይ አታነሣምን?
ምራቄን እንኳ እስክውጥ ፋታ አትሰጠኝምን?
20ሰውን የምትከታተል ሆይ፤
ኀጢአት ብሠራ፣ አንተን ምን አደርግሃለሁ?
ለምን ዒላማህ አደረግኸኝ?
ለምንስ ሸክም ሆንሁብህ?
ጥቂት የማሶሬቲክ ጽሑፍ ቅጆች፣ የጥንት የዕብራውያን ጸሓፍት ትውፊትና ሰብዓ ሊቃናት እንዲሁ ሲሆኑ፣ አብዛኛው የማሶሬቲክ ጽሑፍ ቅጆች ግን ለራሴ ሸክም ሆንሁ ይላሉ።

21መተላለፌን ለምን ይቅር አትልም?
ኀጢአቴንስ ለምን አታስወግድልኝም?
ትቢያ ውስጥ የምጋደምበት ጊዜ ደርሷል፤
ትፈልገኛለህ፤ እኔ ግን የለሁም።”
Copyright information for AmhNASV